Felegetibeb Sunday school EOTC

መግቢያ

የሰንበት ትምህርት ቤቶች አስፈላጊነት

  •     አሁን ባለው የቤተ ክርስቲያናችን ነባራዊ ሁኔታ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ሌሎች የአገልግሎት ማኅበራት በቤተ ክርስቲያኒቱ ሁለንተናዊ አገልግሎትና እድገት ወስጥ እያበረከቱት ያለው አስተዋጽዖ እጅግ ታላቅ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ እነዚህን ማኅበራትና አደረጃጀቶች በአግባቡ በመቆጣጠር ወጥ የሆነ መዋቅራዊ አሰራር እንዲኖራቸው በማስቻል አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ ብትችልና ምቹ የአገልግሎት ዐውድ ብትፈጥርላቸው ለቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ እጅግ ሰፊ መሆን ይችል ነበር፡፡ አሁን ባለው የቤተ ክርስቲያኒቱ ተጨባጭ ሁኔታ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ያላቸው አስፈላጊነት ይህን ይመስላል፡-
  1. የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖያዊና መዋቅራዊ ክፍተት በመሙላት ረገድ ታላቅ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡

  • የቤተክርስቲያናችን አስተዳደር ዘመኑን የዋጀና የተጠናከረ አለመሆኑ፣ የፋይናንስ ስርዐቱም ያልተማከለ መሆኑ አሁን በቤተ ክርስቲያኒቱ ወስጥ ለሚታዩት ችግሮች፣  ለአቢያተ ክርስቲያናት መዘጋት፣ ለአብነት ትምህር ቤቶች መዳከምና ለምእመናን መነጠቅና መወሰድ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ በዚህ ረገድ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በቤተ ክርስቲያኒቱ የሚስተዋሉትን ክፍተቶች በሚችሉት አቅም ለመሙላትና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ረገድ እያደረጉት ያለው አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው፡፡ ለምሳሌም ያህል የአብነት ትምህርት ቤቶችን ለማገዝ የመማሪያ መጻሕፍትን፣ አልባሳትንና ሌሎች የመገልገያ ቁሳቁሶችን በማሟላት ረገድ እያደረጉት ያለው አስተዋፅዖ ከፍተኛ ነው
  1. የወንጌል ተደራሽነትን ለማስፋት ሰንበት ትምህርት ቤቶች ትልቅ አስተዋጽዖ አላቸው፡፡

  • ሰንበት ትምህርት ቤቶች በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ በሚሰጡ ማናቸውም ዓይነት ትምህርቶች ውስጥ በዝግጅትና በማስተማር እያደረጉት ያለው ተሳትፎ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት መስፋፋት፣ መጠናከርና ለተደራሽነቱም ያለው በጎ አስተዋጽዖ በምንም ሊተካ የማይችል ነው፡፡ የአውደ ምህረት ትምህርቶችን፣ ተከታታይ የኮርስ ትምህርቶችንና የርቀት ትምህርቶችን በመቅረፅ፣ በመምራትና በማስፈጸም ደረጃ እያበረከቱት ያለው ድርሻ ለእቅበተ እምነትና ለምእመናን መጠበቅ ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ ኦርቶዶክሳዊውን አስተምህሮ በማስፋፋትና በማጠናከር፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በማዘጋጀትና በመምራት፣ እርስ በርሳቸው በመማማር፣ ህፃናትን፣ ወጣቶችንና ጎልማሶችን በማስተማር ለክርስቶስ ወንጌል መዳረስና ለመንግስቱ መስፋት ሐዋርያዊ ተልዕኳቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡
  1. ሰንበት ትምህርት ቤቶች በጋራ በመሰባሰባቸው በቤተክርቲያን ውስጥ ለሚካሄዱ አገልግሎቶች ውጤታማነት ትልቅ አስተጽኦ ያደርጋሉ፡፡

  • የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በኅብረት ሆነው ለአገልግሎት መሰባሰባቸው አንድ ሰው በግለሰብ ደረጃ ከሚሰራው ስራና ሊያበረክተው ከሚችለው አስተዋጽዖ በተሻለ ደረጃ የሚታይ ለውጥ ለማስመዝገብና የቤተ ክርስቲያኒቱን ሐዋርያዊ አገልግሎት ለመደገፍ ምቹ ሁኔታና ዕድልን ይፈጥራል፡፡ ስራዎችን በዕቅድ፣ በተደራጀና በተጠናከረ መልኩ ለማከናወን፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ባለው አሰራር ውስጥ ሆኖ ሊቆጠርና ሊለካ የሚችል ስራን ለመስራትና ለውጥ ሊያመጣ የሚችል አገልግሎትን ለመፈጸም ሰንበት ትምህርት ቤቶች ምቹ መድረኮች ናቸው፡፡
  1. ሰንበት ትምህርት ቤቶች የእግዚአብሔርን ብዙ የጸጋ ስጦታዎች ለመጠቀም ትልቅ እድል ይሰጣሉ፡፡

  • ሰንበት ትምህርት ቤቶች የነገዋ ቤተ ክርስቲያን ተረካቢ ወጣቶች በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች እንዲሳተፉ እድል በመስጠትና ወጣቶች ያላቸውን ተሰጥኦ ለይተው በየዘርፉ ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን እንዲያገለግሉ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ሁሉም ሰው እንደተሰጠውና እንደበዛለት ጸጋ መጠን የክርስቶስ ወንጌልና የመንግስቱ ሰራተኛ እንዲሆን በማስቻልና ቤተ ክርስቲያንን በልዩ ልዩ የሙያ ዘርፎች ማገልገል እንዲቻል ሰንበት ትምህርት ቤቶች ምቹ የስራ አካባቢዎች ናቸው፡፡
  1. ሰንበት ትምህርት ቤቶች በቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ አገልግሎት ውስጥ ዝግጁነትን ከማሳደግ አንጻር ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡

  • የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎቶች ተደራሽነት ለማሳደግና ለነገው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት አስፈላጊውን ዝግጅት ለማድረግ፣ ወቅቱ የሚጠይቀውን ተጨባጭ ሁኔታ ለመገንዘብና ወቅቱ በሚፈልገው መልኩ የቤተ ክርስቲያናችንን አገልግሎቶች ለመቃኘት፣ ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ጊዜያት ብዙ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች በሚያጋጥሟት ወቅት  እነዚህን   አደጋዎችና ችግሮች እንደዚሁም አፍራሽ እንቅስቃሴዎች ለመግታት ለቤተ ክርስቲያን አባቶች በቂ መረጃዎችን በማሰባሰብ በቀላሉና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአባቶች በመስጠት ቤተ ክርስቲያን አፋጣኝ እርምጅ እንድትወስድ ጉልህ ድርሻ አላቸው፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤት ዓላማ

  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዶግማ፣ ቅኖና፣ እምነትና ሥርዓት ተጠብቆ ሳይበረዝ ሳይከለስ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ

  • ማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታይ የሆነ ምእመን የሃይማኖቱን ሥርዓት በውል እንዲያውቅና እንዲረዳ ማድረግ

  • ወጣቶች የቤተ ክርስቲያንን ሕግና ሥርዓት ተምረው ለሀገርና ለወገን ጠቃሚ፣ መልካምና በሥነ ምግባር የታነፁ ዜጎች እንዲሆኑ ማድረግ

  • በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ (መክ. ፲፪፡፩) የሚለውን የአምላክ ተእዛዝ ወጣቶች እንዲፈጽሙ ማስቻል

  • እነዚህን ከላይ የተዘረዘሩትን አበይት ዓላማዎች ከግብ ለማድረስ ጠንካራ ሰንበት ትምህርት ቤት ያስፈልጋል። ወጣቶችን በሰንበት ትምህርት ቤት ለማሳደግ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የበኩላቸውን መወጣት በእጅጉ አስፈላጊ ነው። አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ጴጥሮስ ከሰጠው መመርያና ትዕዛዝ መካከል ሕፃናትንና ወጣቶችን በሃይማኖት እያስተማረ ለመንግስተ ሰማያት ማብቃት እንደነበር ቅዱስ ዮሐንስ በመጽሐፍ ቅዱስ ጽፎልናል (ዮሐ 21፥15)። የአምላካችንን ትዕዛዝም ትውልድ ሁሉ ይፈጽመው ዘንድ ሕፃናትን እና ወጣቶችን አስተባብሮ ማስተማር የሚችል ሰንበት ትምህርት ቤት ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም።

  • ሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቱን ትውልድ በአምልኮተ እግዚአብሔርን አፅንቶ በሃይማኖትና በምግባር ከማኖርም ባሻገር ለቤተ ክርስቲያን ቀናኢ የሆኑ አገልጋዮችን አፍርቷል፤ በማፍራት ላይም ይገኛል። ሰንበት ትምህርት ቤት በዕለተ ሰንበትና አበይት በዓላት ወቅት ያሬዳዊ መዝሙራትን ከማቅረብም በላይ ዲያቆናትን፣ ቀሳውስትን፣ ቆሞሳትን፣ ጳጳሳትን፣ መምህራነ ወንጌልን፣ ሰባኪያንን እና በልዩ ልዩ አገልግሎት ላይ የሚፋጠኑ ዘመኑን የዋጁ አገልጋዮችን ለቤተ ክርስቲያናችን አበርክቷል። ይህ አገልግሎት እንዳይቋረጥና ቤተ ክርስቲያን ለትውልድ ሁሉ ከነሙሉ ክብሯ ትተላለፍ ዘንድ በያለንበት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሰንበት ትምህርት ቤትን ማጠናከር የዘወትር ተግባር ሊሆን ይገባል። በተለይ በዚህ በውጭው ዓለም ልጆቻችንን የምዕራቡ ባህልና እምነትየለሽ ዘመናዊነት እንዳያጠቃቸው በሰንበት ትምህርት ቤት አስመዝግበን ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ እንዲያውቋት ማድረግና በሃይማኖትና በምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ ማስቻል የወላጅ ሃይማኖታዊ ግዴታ መሆን አለበት። ምክንያቱም ልጆቻችን ኦርቶዶክሳዊት እምነትን፣ ዶግማን፣ ሥርዓት እና ትውፊትን በሰንበት ት/ቤት ካልተማሩ ሃይማኖታችንን ጠብቀውና አስጠብቀው ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ አይቻላቸውም፡፡

  • በአጠቃላይ ሰንበት ትምህርት ቤት ትውልድን ለመቅረጽ የሚሰጠው ጠቀሜታ ታላቅ ስለሆነ ወጣቶችና ሕፃናት በሰንበት ትምህርት ቤት የሚሰጠውን መደበኛ ትምህርት መከታተል እንዲችሉ ማድረግና በማነኛውም ጊዜና ቦታ አርያና ምሳሌ ሁነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነትና ሥርዓት አፅንተው ይይዙ ዘንድ ከሁልጊዜውም በተለየ መልኩ የሁላችንም ድጋፍ እንደሚያስፈልግ መረዳትና በመተግበርም እግዚአብሔር አምላክ የሰጠንን ሃይማኖታዊ ተልእኮ መፈጸም ይጠበቅብናል።

  • በሰንበት ት/ቤት ያደጉ ልጆች በሚሰማሩበት ሥፍራ የተሳካላቸውና በማኅበራዊ ሕይወት የተዋጣላቸው መሆናቸው ሰንበት ት/ቤት መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ መሆኗን ያረጋግጣል፡፡ ሰንበት ት/ቤት ሥራ አስለምዳና ጸባይ አርማ ወደ ስኬት ተራራ የምታወጣን ደግ እናትን ትመስላለች፡፡ አበው እንደሚሉት እሳት ያልነካው ሸክላና በሰንበት ት/ቤት ያልተማረ ወጣት አንድ ናቸው፡፡

የደ/ዘ/ደ/መ/ቅ/ሚካኤል ቤ/ክ በእግዚአብሔር ፈቃድ ቤ/ክ በእግዚአብሔር ፈቃድ በ1989ዓ.ም ተመሰረተ፡፡ቤ/ክ በተመሰረተ በሰባተኛው ቀን በጥቅት አባላት የደ/መ/ቅ/ሚካኤል ቤ/ክ ፈለገ ጥበብ ሰ/ት/ቤት ተመሰረተ፡፡ ሰ/ት/ቤቱ ተመስሮት በ1992 ዓ.ም የእራሱ ደንብና መመሪያ ኖሮት በቃለ ዓዋዲው መሰረት በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስር የተለያዩ ክፍሎችን በማዋቀር አገልግሎቱን በተጠናከረ መልኩ ሲሰጥ ነበር እየሰጠ ይገኛል፡፡ ሰ/ት/ቤት በን/ክፍላት መዋቀሩ አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ በስራ አመራሩ መመሪያ መሰረት ይኼ የተግባርና ኃላፊነት እንዲዘጋጅለት ሆኗል፡፡

ተጠሪነት

  • በደ/ዘ/ደ/መ/ቅ/ሚካኤል ቤ/ክ ፈለገ ጥበብ ሰ/ት/ቤት ተጠሪነቱ ለደብሩ ሰበካ ጉባኤ ሲሆን ሁሉም የአገልግሎት ክፍላት ተጠሪነታቸው ለስራ አመራር ጉባኤ ሆኖ የሰ/ት/ቤቱ ቁጥጥር ክፍል ግን ለሰ/ት/ቤቱ ጠቅላላ ይሆናል፡፡

የሰ/ት/ቤቱ ዓላማዎች

  •  በደብረ ዘይት ከተማ የሚኖሩ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ወጣቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነት፣ ሥርዓትና ትውፊት ኢንዲማሩ ማድረግ
  •  ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላት ጋር በመተባበር ትምህርተ ወንጌልን በተለያዩ ዘዴ ኢንዲስፋፋ ማድረግና ወጣት ሰባኪያንን ማፍራትና ማበረታታት፡፡
  •  የቤተ ክርስቲያኒቷን ሊቃውንት ዝናና ክብር ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግና
  •  ከአባላቱና ከተለያዩ የገቢ ምንጮች በሚገኘው ገቢ ልዩ ልዩ የበጎ አድራጎት ስራ መስራት ናቸው፡፡

አቋም

  •  በማንኛውም የፖስቲካ አንቅስቃሴ ውስጥ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት የስሙም፡፡

አባላት

  • በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የስላሴን ልጅነት ተቀብለው በቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አምነት አኝተው ወጣቶች በአጥቢያ ሰንበት ት/ቤቶች መርሐግብር ሲከታተሉ ቆይተው በዝውውር ወይም ከየተቋማቱ ተመርቀው ከመጡ በኋሳ የሰንበት ትምህርት ቤት ወይም የሰበካ ጉባኤ አባል ሆነው መንፈሳዊ አገልግሎት የሚፈጽሙ
  • ለሰ/ት/ቤቱ ዓላማ ተግባራዊነት በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸውና ጉልበታቸው የሚራዱና በአባላት ክትትልና ግንኙነት ክፍል በአባልነት የተመዘገቡ ክርስቲያኖች መሆን አለባቸው፡፡

አገልግሎትና አገልጋይ

  • አዲስ ወደ ሰ/ት/ቤት ያገቡ አባላት በትምህርትና ስልጠና ክፍል የሚሰጠውን የአንደኛ ዙር ተከታታይ ትምህርት የወሰዱና ቢያንስ አንድ አመት ቆይታ ያላቸው (በአባላት ክትትልና ግንኙነት ክፍል ከተመዘገቡበት ቀን እንስቶ አንድ አመት )፡፡
  •  በአገልግሎት ክፍሎች የሚጠበቅበትን/ባትን የአገልግሎት ቅድመ ሁኔታዎችን ያሟላ/ች እንዲሁም በማንኛውም ሁኔታ በአባላቱና ሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ ጥሩ ምሳሌነት (በአስባበስ፣ የጸጉር አያያዝ፣ወዘተ) ያለው/ት፡፡
  • በሰ/ት/ቤት መርሐግብራት ማለትም ትምህርት፣ ጸሎት፣ በተመደቡበት የአገልግሎት ክፍላት፣ ዝክር አና የአንድነት መርሐግብራት ያለ ነውርና ያለ ነቀፌታ በንቃት የሚሳተፍ፡፡
  • አንድ አገልጋይ አንደሚያገለግልና አንደማያገለግል የሚወሰነው ከሚመለከታቸው የአገልግሎት ክፍላት መረጃው በአባላት ክትትልና ግንኙነት ክፍል ቀርቦ ሲፈቀድለት ብቻ ይሆናል፡፡ ስዚህም የአባላት ክትትልና ግንኙነት ክፍል አገልግሎት በተፈለገበት ወቅት መረጃውን ቢያንስ ከአንድ ሳምንት በፊት በእራሱ ፊርማ ይለጥፋል፡፡
  • ቅሬታ ያለሙ አባል ካል የአገልጋይ ስም ዝርዝር ከተስጠፈ በሶስት ቀናት ውስጥ ቀርቦ ጉዳዩ በአባላት ክትትልና ግንኙነት ክፍል እንዲታይለት ማድረግ ይችላል፡፡

ምርጫን በተመለከተ

  • የሰ/ት/ቤት ስራ አመራር በየሶስት አመት የሚደረግ ሲሆን የደብራችን ሰ/ጉባኤ ምርጫ በተደረገ በዓመቱ በስድስተኛው የሰ/ት/ቤት ጠቅላላ ጉባኤ ይደረጋል፡፡ በአገልግሎት ላይ ያለው ስራ አመራር በልዩ ልዩ አገልግሎት በመመደብ እና በማሰልጠን ያበቃቸውን 14 ዕጩዎችን መርጦ ለአስመራጭ ኮሚቴ ያቀርባል፡፡ የደብሩ የሰበካ ጉባኤ ተወካዮች ከሶስት የማያንሱ ከአምስት የማይበልጡ አስመራጮችን ካስመረጠ በኋላ አስመራጭ ኮሚቴው ለተወሰነ ጊዜ በነበራ አመራር የቀረበለትን ዕጩዎችን እንዲሁም አስፈላጊ ሆነ ካገኘው ተጨማሪ ዕጩዎች ካጠናና ከገመገመ በኋላ በዕለቱ ወይም በሌላ ቀን ለጠቅላላ ጉባኤ ያቀርብና ምርጫው ይካሄዳል፡፡ ምርጫውን በድምጽ/በዕጣ ሲሆን ይችላል፡፡

ስብሰባን በተመለከተ

  •  የሰ/ትቤቱ አመራር ጉባኤ በአስራ አምስት ቀን አንድ ቀን ይሰበሰባሉ
  •  የክፍላት በአስራ አምስት አንዴ ይሰበሰባሉ
  •  በሰ/ት/ቤት የተቋቋሙት ኮሚቴዎች በወር አንድ ቀን ይሰበሰባሉ
  •  በስድስት ወር አንዴ የአባላት ወላጆች ይሰበሰባሉ
  •  የሰ/ት/ቤት አባላት በአመት ሁለት ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ ያደርጋሉ
  •  የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ በየካቲትና ሐምሌ ወር ይደረጋል

የስብሰባ ተሳትፎን በተመለከተ

  • ከግማሽ በላይ ተሳታፊዎች ከተገኙ የክፍል፣ የን/ክፍላት፣ የኮሚቴና የጠ/ጉባኤ ስብሰባው ይካሄዳል
  • በስብሰባው ቁጥጥር ክፍል ድምጽ አይኖረውም በቃለ ጉባኤም ላይ አይፈርምም በማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ ላይ ጠቅላላ ጉባኤ ወክሎ መመሪያ ያስተላልፋል ሐሳብ ይሰጣል የተወሰኑት ውሳኖዎችን ተግባራዊነትና የሰ/ት/ቤቱ ደንብ መከበርን ይከታተላል፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘና የአመራር ጉባኤ ተቀባይነት ካገኘ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ ያደርጋል።

የጠቅላላ ጉባኤ አባላት

  • የፈለገ ጥበብ ሰ/ት/ቤት አባላት፣ የወላጅ ኮሚቴና ተወካዮች፣ የሰ/ካጉባኤ ተወካዮች ሲሆኑ ስራ አመራሩ ለጠቅላላ ለጉባኤው ግብዓት ሊሆኑ ይችላሉ የሚላቸውን ሌሎች ተጋባዥ እንግዶችን እንደየ አስፈላጊነት ሊጠራ ይችላል፡፡

የአባላት ከአገልግሎት መታገድ

ከላይ በአባልና አባልነት ስር በተዘረዘረው መስፈርት መሰረት አባል ከሆኑ በኋላ ከሰ/ት/ቤት አባል የማይጠበቅ ኢ-ክርስቲያናዊ ተግባር ከታየበት ከዚህ በታች በቀረበው መሰረት አርምጃ ይወሰድበታል፡፡

  1. ከኦርቶዶክስ እምነት ውጪ የሌላ አምነት ሲከተል ወይም በሌሎች የእምነት ድርጅቶች ሥርአተ አምልኮ ሲሳተፍ አንድ አባስ ከተገኘ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከማንኛውም አገልግሎት ለአመራር ጉባኤ በአባላት ክትትልና ግንኙነት ክፍል አቅራቢነት ታግዶ በሰ/ጉባኤ በኩል ቀኖና አንዲ ሰጠው ይደረግና ከተመለሰ እንደገና እንደ አዲስ አባል ተመዝግቦ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡ የማይመለስ ከሆነ ግን አገዳሙ ጸንቶ ከአባልነት ይሰረዛል፡፡
  2. በቤ/ክ በተከለከሉት ማንኛውም መጥፎ ስነምግባር ማለት ጫት መቃም፣ ማጨስ፣ መስከር፣ ዝሙት ወዘተ እንዲሁም በማኛውም ኢ-ክርስቲያናዊ በሆነ ቦታ (ጭፈራ ቤት፣ ሺሻ ቤት፣ እና ተያያዥነት ባላቸው ቦታዎች) አንድ አባል ቢገኝ በአባላት ክትትልና ግንኙነት ክፍል ምክር አገልግሎት ክፍል ለብቻው እንዲመከር ይደረጋል፡፡ በዚህ መልኩ ተሞክሮ የማይመለስ ከሆነ በአባላት ክትትልና ግንኙነት ክፍል በክፍል ደረጃ ይመከራል፡፡ አባሉ በዚሁ ከቀጠለ በሰ/ት/ቤቱ ንስሐ አባት እንዲመከር ተደርጎ የማይመለስ ከሆነ ከአገልግሎቱ እንታገድ እና እንዲማር ይደረጋል፡፡ ከዚህ ሁሉ ጥረት በኋላ አባሉ የማይመለስ ከሆነ (1) ላይ የተቀመጠው የመጨረሻው እርምጃ ይወሰድበታል፡፡
  3. በሌላ በኩል የአገልግሎት ክፍላት ከዚህ ደንብ ጋር በማይጋጭ መልኩ አዘጋጅተው በስራ አመራር ጉባኤ በጸደቀላቸው የውስጠ ደንብ መሰረት አባላት በየአገልግሎት ክፍላቸው የእርምት እርምጃ በክፍላት ደረጃ የሚወሰድባቸው ሲሆን ጉዳዩ ሃይማታዊ ጉዳይ ሆኑ የማይፈታ ከሆነ (1) ላይ የተቀመጠው እርምጃ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን ጉዳዩ የስነ ምግባር ጉዳይ ሆኖ በክፍል ደረጃ የማይስተካከል ከሆነ (2) ላይ ያለው እርምጃ ተግባራዊ ይሆናል፡፡